የአፄ ምኒልክ ፪  ደብዳቤ :  ዓድዋ እና የህዳሴው ግድብ

የአፄ ምኒልክ ፪  ደብዳቤ :  ዓድዋ እና የህዳሴው ግድብ

ተፃፈ ከአፄ ምንሊክ ሁለተኛ

(ታላቁ የህዳሴው ግድብ የዚህ ትውልድ አድዋ ነው)

ውድ የሀገሬ ህዝብ ሆይ፣

በተዋበ ክብርና አግራሞት እኔ ምንሊክ ሁለተኛ ስለ እናንተ ከልቤ የገባውን እውነት እንዲህ ሰድጄላችሁዋለሁ: የመንግስታችንን አንድነትና የህዝባችንን አብነት ዳግም እንዳፀናንበት የሺ ስምንት መቶ ሰማንያ ስድስት ዓ.ምቱ ታሪካዊ ድል  ይህም ትውልድ የአባይ ወንዛችንን በማቀብ የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመሳሳይ የቁርጠኝነት መንፈስና ህብረት ሲተጋበት ባየሁኝ ጊዜ እጅግ ደስ አለኝ። በእኛው ዘመን ህዝባችንን ክተት ብለን ከሮም የተላከብንን የጣሊያን ወራሪ በ1888 ዓ.ም አምላክ ኃይልን ጨምሮልን በአድዋ አምባዎች ልኩን ሰጥተነው መንግስታችንን በነፃነት እንዳቆየነው ሁሉ እናንተም አደራ ተቀባዮቻችን በብርቱ ፅናትና ጥንካሬ ታላቁን ግድብ ገንብታችሁ ወንዛችንን ወደ ፋና በጭማሪውም ወደጉልበት ለመቀየር ጫፍ መድረሳችሁ ለእናንተም ሆነ ከእናንተ በሁዋላ ለሚከተላችሁ ወገን ሁሉ የሚያበረክተው  ፋይዳ ዘርዝሬ የምጨርሰው አይሆንም።

አድዋ  ውድ የሀገራችን ልጆች ለመንግስታቸውና ለቃሌ ታምነው የመንግስታችንን ነፃነትና የሀገራችንን ዳር ድንበር በደማቸው ጠብቀው ያቆዩበት የኔ ዘመን ተጠቃሽ ትልቅ ገድል ነው። ዛሬም የኛ ተረካቢዎች የሆናችሁት እናንተም አምላክ የቸረንን ወንዛችንን በማቀብና የታላቁ ህዳሴ ግድብን በመስራት ጉዳይ እያሳያችሁት ያለው ርብርብ ለፈረንጅ አሽከርነት የማትመቹ መላው ህዝባችንን በብርሃን የምታንቦጎቡጉ የሀገራችሁን ዕድገትና ከፍታ የምትገልጡ ልትሆኑ ዕድልን ተችራችሁዋል።

የአድዋ ድል ልክ የነጭ ተስፋፊዎችን እብሪት ልክ ያስገባንበት ታሪካዊ ድላችን እንደሆነው ሁሉ ታላቁ የህዳሴ ግድብም ዳግም ሊወሩን እያሴሩ ካሉት ኢሮፓውያን ጋር ካለ ነፍጥ የምታደርጉትን ትግል ይወክላል። እናም አሳልፈን የሰጠናችሁን አደራ ጠብቃችሁ ማኖርና ሀገራችንን ማስከበር ግዴታችሁ ሆኗል። የአድዋ ድል ፋይዳ ከኛ አልፎ ለበዙ አፍሪቃውያንም ከፈረንጅ አገዛዝ ነፃ እንዲወጡ ያበረታና መንገድ ያበጀላቸው መሆኑንም የሚታወቅ ነው። በተመሳሳይም ታላቁ የህዳሴ ግድብ የክፍለ-አህጉሩን የሃይል ቁመና የቀየረና የአፍሪካ ሀገራት ምድር የለገሰቻቸውን በረከትና ሀብቶች ለራሳቸው ብልፅግና የሚጠቀሙበት ከፈረንጅ ዳግም ወረራና ልግዛህ ባይነት ተጠብቀው በራሳቸው ፈቃድ እንዲኖሩ የሚያስችል ፀጋና አቅም ነው።

ከፈረንጅ አስገዳጅነት ነፃ የመሆን ጉዞ ገና መጀመሩ መሆኑን እገነዘባለሁ። በህዳሴው ግድብ መሪነት የምታደርጉት ይህ ጉዞ ግን የህዝባችን ኩራትና አንድነት መገለጫ መሆን በፍፁም አልጠራጠርም። በአድዋ ጦርነት ከኢጣልያ ወራሪ ጦር ጋር በመተናነቅ የመንግስታችንን ጥቅም ያስከበርንበትን አቅሞ ለአለም አሳይተንበትም የለ። ዛሬም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሀገራችን በፈጣሪ ችሮታ የተሰጣትን በረከቶች እንደሚያስረዳ  ለስኬታማነቱም ህዝባችን በቁርጠኝነት እያበረከቱት ያለው ድጋፍና ርብርብ የህዝባችንን ፅናትና የታላቅነታችን የማይናወፅ ሩጫችንን ማሳያ እንዲሆን እንዳበቃው አስታውቃችሁዋለሁ።

አድዋ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ኃይልና መተጋገዝ ተምሳሌት መሆኑ ሀቅ ነው። የመላው ህዝባችን የጋራ ጥረትና ድጋፍ የድላችን ፅኑ መሠረት ነበር። በህዳሴው ግድብም በእያንዳንዱ የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች ያደረጉት ድጋፍና አበርክቶ በተመለከትኩ ጊዜ ልቤ ደስ ይለዋል። በግድቡ ፕርጀክት ዙሪያ ያሳያችሁት ህብረትና ቁርጠኝነት እጅግ የገዘፈ ነው። የግድቡ ስኬታማነት ዋነኛው መንስዔም ይሄው ይሄው ትብብርና ጥረታችሁ ነው።

በአድዋው ጦርነት ወቅት ከሀገራችን ጥቅምና ዳር ድንበር በተቃርኖ ከውጭ ሀይሎች ተፈፅሞብን የነበረውን ተቃውሞና ጫናም ዛሬም ድረስ በልባችን አለ። በተመሳሳይ መልኩ ዛሬም ታዲያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ግብፅና ሱዳን በምዕራባዊያን ጫንቃ ታግዘው ተቃውሞ የበረከተበት ሆኗል። ይህ ተቃውሞም ከብሔራዊ ጥቅማችንንና ሉዓላዊነታችን ላይ በውጭ ሃይሎች የሚደረግብንን ጫናና ፈተናዎችን ከመወጣት አንፃር በፅናት መቆም እንዳለብን ትልቅ ማሳያ ነው። ስለሀገራችን ጥቅሞችና ሉዓላዊነታችን በፅናት ታገሉ። ከጎረቤት ሀገራት ጋርም ሁሉንም ተጠቃሚ ለሚያደርግ መፍትሄዎችም ጣሩ!

የናንተ ትውልድ ዳግማዊ የአድዋ ገድል ተደርጎ በሚመሰለው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ፈታኝ እንቅፋቶችን ታግሎና ነቅሎ ድል የማድረግ ወኪል እንድትሆኑ አብቅቷችሁዋል።  አድዋ ኃያል የኢሮፕ ቅኝ ገዢ ተስፋፊ መንግስታትን ታግሎ ድል ማድረግ መቻሉን ለአለም እንደገለጠው ሁሉ  የህዳሴው ግድብም የፋይናንስ ድጎማና አለሜቀፍ የዲፕሎማሲ ጫና ማሸነፍ እንደሚቻል ያሳየ ሆኗል። ይሁና  እንጂ ሁለቱም ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያውያንን መንፈስ የበለጠ በማነቃቃትና ፈተናዎችን በማሸነፍ ቁርጠኝነት በተከታታይና ቀጣይነት ብዙ ትጋትን የሚጠይቁ መሆናቸውን ግን አትዘንጉ። የቀደመው የአድዋ ድልና የዘመናችሁ የአድዋ ተምሳሌት የህዳሴው ግድብ የወል ግባችንን ለማሳካት አንቂ መንፈስ ይሁናችሁ።

በተጨማሪም የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጪውን የኢትዮጵያ እና ክፍለ አህጉር ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ቅርፅ የማስያዝ አቅምን የተላበሰ ነው። የአድዋው ድል ኢትዮጵያ ሀገራችንን ሉዓላዊ ነፃነት እንዳስጠበቀውና የአፍሪካውያንን የነፃነት ትግል እንዳቀጣጠለው ሁሉ ታላቁ ግድባችንም ኢኮኖሚያችንን እና በአካባቢያችን ያለንን ተሰሚነት የሚያመነድገው ይሆናል። በእነዚህ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የጠራ ራዕይና ለተሻለ ስኬታማነት የህዝባችንን የወል ድጋፍና ጥረት ገንቢ ማዕቀፍ የሚሆኑ ናቸው።

አድዋ ፅናታችንን እና ፈተናዎችን ታግሎ የማሸነፍ ብቃታችንን ለአለም አስመስክሯል። የግድቡ ፕሮጀክትም ለሃገራዊ ለውጥ የማይናወፅ ቁርጠኛነታችሁን የምታስመሰክሩበት ዕድልን የፈጠረላችሁ ሆኗል። የምንወዳትን ኢትዮጵያ ሀገራችንን የበለፀገችና ደህንነቷ በተረጋገጠ ኩሩ ሀገርነት ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ዕቅዳችን ዋነኛ መሠረት የታላቁ ህዳሴ ግድብን በስኬት ዳር የማድረስ ትግላችን ላይ የተንጠለጠለ ነው። የግድቡ ሰፊ ታዳሽና ወጥ  የኤሌክትሪክ ሀይል የማመንጨት ርብርባችን የሀገራችንን የሀይል ፍላጎት ከማሳለጥ በተሻገረ ለኢንዱስትሪ ዕድገት የስራ ዕድል ፈጠራና ለተረጋጋ ኢኮኖሚ ማንበር ምቹ መደላደልንም የሚፈጥር ነው። ሀብቶቻችንን በተገቢ ጥቅም ላይ በማዋል ነፃነታችንን ማረጋገጥና የዜጎቻችንን ደህንነት ማረጋገጥም ይጠበቅብናል።

በመጨረሻም የታሪካዊው የአድዋ እንዴት የአሁኗን ሀገራችንን ብሄራዊ ማንነትና ክብር በጥንካሬ መሠረት ላይ እንዳኖረ እንድናስታውስ እሻለሁ። የህዳሴው ግድብ የሚዳሰስ አካላዊ ገፅታው ባሻገር የታላቅነትና አንድነታችን ተምሳሌትና የመቻቻል ዕሴቶቻችን ማሳያም ጭምር ነው። ይህ ግድብ የምህንድስና ባለሙያዎችን ሌሎች ሰራተኞችንና የመላው ህዝባችንን አበርክቶ በአንድ ያስተሳሰረ ብሎም በጋራ ህልምና ግብ ስሜት ያዋሀደ የትውልዱ ገድል የመሆኑ ምስክር በመሆኔ ልቤ በሀሴት ተመልቷል። በሀገራዊ ልማትን የማፋጠንና የራስን አቅም የማዳበር ጉዞአችን ውስጥ ሰፊ አቅም የፈጠረውን ይህን ግድብ  እንደ አንድነታችሁ ተምሳሌት ተጠቀሙበት።

እንዲህ እላችሁዋለሁ።

ያለፈው ትውልድ ያስረከባችሁን ሀገራዊ አደራ በማስቀጠል መንፈስ ተመልታችሁ የሀገራችንን ሉዓላዊነትና ቀጣይ ብልፅግና እውን ለማድረግ በጀመራችሁት አንድነት ቁርጠኝነትና ፅናት እንድትቀጥሉ አበረታችሁዋለው።

ታላቁ የህዳሴው ግድብ የዘመናችሁ አድዌ ነው።

አፄ ምንሊክ ሁለተኛ